የመከላከያ መግለጫና የአፋር ህዝብ ዋይታ: እውነቱ የቱ ጋር ነው?

(Cammadí Macammad)

እንደ መነሻ

ይህ ፅሁፍ ትናንት ወዲያ የ"ኦብኖን ጭፍጨፋ" በማስመለከት የመከላከያ ሚኒስቴር የሰጠው መግለጫ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው። ነገር ግን ሰለ ጉዳዩ ጠለቅ ያለ ነገር እንድታውቁ በማሰብ ሁለት ምንጮችን ልጋብዛችሁ ወደድኩኝ።

1. ዶር ያሲን መሀመድ ያሲን " Regional dynamics of inter-ethinic conflicts in the horn of Africa: An analysis of the Afar-Somali conflict in Ethiopia and Djibouti" በሚል ርዕስ ለሦስተኛ ድግሪ ማሟያነት ያቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ (ጎግል ማድረግ ይቻላል)

2. ወዳጄ ሀጅ አሎ ያዬ መሀመድ "መፍትሔ አልባው የአፋር-ሱማሌ (ኢሳ) ግጭት" በሚል ርዕስ በቅርቡ ያወጣው በማስረጃ የተጠናቀረ መፅሐፍ (አሁን ገባያ ላይ ይገኛል)

ሁለቱንም ካነበባችሁ በኋላ ግጭቱን "ተራ የግጦሽና የውሃ ግጭት" አድርጎ የሚያቀርበው መከላከያ ሚኒስቴርን (እንደ አገር ያለ አቋም ነው በገራችን ላይ) በደንብ እንደሚትታዘቡት እተማመናለሁ።

መግቢያ

በአፋር እና ኢሳ ግጭት የሚታወቀውና አስርታት አመታትን ያስቆጠረው የአፋር–ሱማሌ ጂኦፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጦርነት በአዲስ መልኩ ካገረሸ አስረኛ ወር ይዘናል። የፅሁፌ ማጠንጠኛ የሚሆነው ያሁኑ ግጭት አነሳስ፣ መንስኤውና ሂደቱን ነው። ትኩረቴም የመከላከያ ሚኒስቴር ለጅቡቲ መንግስት ጠበቃ በመሆን ላቀረበው መግለጫ መልስ መስጠት ስሆን የሚጠቀማቸው ማስረጃዎች እዚህ ማህበራዊ ድረገፅ ላይ ስዘዋወሩ የቆዩና ለአቤቱታ ስንጠቀምባቸው የነበርናቸው ምስሎችና ፅሁፎች ናቸው።

1. የግጭቱ አነሳስና የጅቡቲ መንግስት ሚና

የኢሳ ጎሳ "እኛ ሱማሌን ነን እንጅ አፋር አይደለንም" በማለት ሰልፍ ማካሄድ የጀመሩት የአፋር ክልል አድስ አመራር በተሾመ በሳምንቱ ነበር። ሰልፉን የጀመሩት የአፋር ክልል ባንድራን በማቃጠል "እኛ ሱማሌ ነን፣ ወደ ሱማሌ ክልል መካለል አለብን" በሚል ነበር። (ፎቶ 1ና 2)
በሰዓቱ ሰላም ለማስከር በተንቀሳቀሰው የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ላይ ቶክስ በመክፈትና በልፅ ጦርነት በማወጅ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከጋላዕሉ እስከ አፋምቦ (3 ዞን የሚያካልል) ቀጠና ላይ ጦርነት ከፈቱ።
ይህ የጦርነቱ አጀማመር በድንገት የተፈጠረ ሳይሆን በደንብ ታቅዶበትና ተዘጋጅቶበት መሆኑን በግልፅ ያሳየ ክስተት ነበር።

1.1. ከዛ በፊት ባሉ ወራት ምን ስካሄድ እንደነበር ትንሽ እንፈትሽ!

የእስማኤል ኡመር ጌሌ (IOG) መንግስት በኢትዬጵያ ላይ የተከሰተው የለውጥ እንቅስቃሴ ከመጀመሪያ ጀምሮ አልተዋጠለትም ነበር። መሆኑ ካልቀረ ግን የራሱን ጥቅም በለውጡ ውስጥ እንዴት መሳካት እንደሚችል በደንብ ስያጠና ነበር። ትኩረቱን ያደረገው በሱማሌ ክልል፣ በአፋር ክልልና በድሬዳዋ ነበር። መጀመሪያ የሱማሌ ክልል ብጥብጥ ውስጥ በነበረ ግዜ ኦጋሶች (የኢሳና የሱማሌ የአገር ሽማግሌዎች) ድሬዳዋ ላይ ባካሄዱት ስብሰባ የጅቡቲው ፕሬዝዴንት አቶ እስማኤል ተገኝቶ ነበር። በሰዓቱ ቀጣዩ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዴንት ከኢሳ ጎሳ ለማድረግ እንቅስቃሴ አስጀመረ።

ሆኖም ግን እቅዱ ሳይሳካለት ሰለቀረ (ምክትል ፕሬዝዴንትነት ብያገኝም) ድሬዳዋንና የአፋር ክልልን መበጥበጥ ቀጣይ አቅጣጫ አድርጎ አስቀመጠ። የዚህ እንቅስቃሴ አጭር ግዜ እቅዱ ሦስት ነበር። አንደኛ የአፍሪካ ቀንድ የ"ሰላም አባት" ማዕረግነቱን የነጠቀው ዶር አብይ መንግስት እንዳይረጋጋ በማድረግ ወላፈኑን መቅበር (samuel hunghinton, The Third wave በሚለው መፅሓፉ ያንድ አገር መንግስታዊ ለውጥ በጎረቤት አገሮች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የማስከተል እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳል፤ በተለይ ድክተተር መንግስታት ከሆኑ) ሁለተኛ ኢትዬጵያ ላይ የሚፈጠረው የኢሳና አፋር ግጭት፡ ጅቡቲ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሰላለው ሁለቱም ማህበረሰብ መሃል በሚፈጠረው ጥሪጣሬ (ግጭት) የስልጣኑን እድሜ ማራዘም ስሆን በሦስተኛ ደረጃ የአፋር ክልል ወደ ብልፅግና መንገድ እንዳይጀምር ማድረግ ነው። የኢትዬጵያ አፋር ካደገ የጅቡቲ አፋሮች እገዛ ያገኛሉ ብሎ ሰለሚያስብ። የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ የአዋሽ ወንዝንና የኢትዬ ጅቡቲን መንገድ ማዕከል ያደረገ የሲቲ ክልል በማቋቋም፣ ለጅቡቲ መንግስት ደጀን የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ኢትዬጵያ ውስጥ እንድኖራቸው (ኢሳዎች) ማድረግ ነው።

1.2. የደህንነት መረጃ
አቶ እስማዕል የሱማሌ ክልል እቅድ ከከሸፈበት በኃላ ቀጥታ ጉዳዬ ብሎ የያዘው የኢሳና የአፋር ግጭትን መቀስቀስ ነው። ለዚህ ዕቅድ የመጀመሪያ ስራ የሆነው የበርበርታ ወጣቶችን ማደራጀት ነበር። የበርበርታ ወጣቶች መንፈሳዊ አባት የኢሳው ኦጋስ ስሆን የውትድርና አዛዣቸው የፕሬዝዴንት ኢስማዒል የሪፕብለካን ጋርድ አዛዥ የሆነው ጀነራል መሀመድ ጃማዕ ነው። የወጣቶች አደራጆች ደግሞ ኡስማንና መስላህ (ኡስማን በኡንዳፎኦ አካባቢ የሽብር ስራ ስሰራ ተይዞ አሁን እስር ቤት ይገኛል።) የተባሉ ወጣቶች ናቸው።

እነዚህ ሁለቱ ወጣቶች ወደ ጅቡቲ የተጠሩት ዶር አብይ ወደ ጅቡቲ ከመሄዱ አንድ ሳምንት በፊት ነበር። በፕሬዝዴንት ኢስማኤል ቢሮ ለ12 ሰዓት የቆዩ ስሆን የጦርነቱን ሙሉ ዕቅድ በጀነራል መሀመድ ጃማዕ በኩል እንድሰጣቸው የተደረገው በዛ ቀን ነው። (ፎቶዎችን ይመልከቱ)። በሁለተኛ ግዜ ደግሞ መሰላህና ኦጋሱ ወደ ጅቡቲ ድጋሜ በመሄድ የተሰሩ ስራዎችን የገመገሙ ስሆን ኮንሰርት ተዘጋጅቶለት የብር ማሰባሰብ ተደርጓል። ከዛ በኃላ መስላህና ጀናራል መሀመድ ወደ ኢትዬጵያ አብሮ ነበር የተመለሱት። (ፎቶውን ይመልከቱ)። መሳለህና ኡስማን በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ለአራት ወራት ዝግጅት ስያካሄዱ ከቆዩ በኃላ (ፎቶዎችን ይመልከቱ) ግጭቱን ለማስነሳት አመቺ ሆኖ ያገኙት ግዜ የክልሉ አመራሮች የስልጣን ርክክብ ባደረጉ በሳምነቱ ነበር።

ከዛ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በሦስቱም ዞን ላይ ወረራ እያካሄዱ ስሆን ጦርነቱ ላይ የሱማሌላንድ፣ የጅቡቲና የሱማሌ ክልል በሰው ኃይልና በሎጂስቲክ እገዛ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆናቸው ተረጋግጧል። ለዚህ ለማስረጃ የሚናቀርበው ከላይ ከቀረበው በተጨማሪ በግጭቱ ግዜ ከተማረኩ መኪኖች ላይ የተገኘ ማስረጃ (ባንድራ፣ የሱመሌለንድ ተረጋ ያለው መኪና፣ ጭንብል፣ ዩኒፎርም እንድሁም መታወቂያ… ከስር በፎቶ ይመልከቱ) ስሆን አለም አቀፍ ሚድያዎች ደግሞ የአገራቱ ተሳትፎ ገልፇል። ከነዚህ መካከል indean ocean letter ጋዜጣ (ከስር በፎቶ ተያይዟል) ና የፋራንሳይ ፓርላማ ሪፖርት ( https://www.facebook.com/AfarTelevisionAf/videos/482449222604588/) ተጠቃሽ ናቸው።

2. የተሞከሩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና ግድፈቶቻቸው

በግጭቱ ከተነሳ በኋላ የክልሉ መንግስት ልዩ ኃይሉን ወደ ቦታው በመላክ የሰላም ማስከበር ስራውን ለመወጣት ብሞክርም ከኢሳ ታጣቂዎች በኩል ቶክስ ሰለተከፈተባቸው ለጊዜው የፌዴራል ፖሊስና የአገር መከለከያ እንድገባ በማድረግ (በአስፋልት ላይ ብቻ) ካረጋጉ በኋላ የሰላም ሚኒስቴር በሰጠው አቅጣጫ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ቦታው ለቆ እንድወጣና ቀጠናው ባልታወጀ አስቾካይ አዋጅ ስር እንድትተዳደር ተደርጓል። በሰዓቱ የተባለው በ15 ቀን ጊዜ ገደብ አካባቢውን ከኮንቶሮባንድስቶችና ከሰርጎ ገብ ታጠቂዎች አፅድተን ለክልሉ መንግስት እናስረክባለን የሚል የነበረ ስሆን የተደረገው ግን በተቃራኒው ነበር። አካባቢው የባሰ ለኮንትሮባንድ አመቺ ከማደረጉም በላይ የኢሳ ታጣቂዎች ቦታውን ተቆጣጥሮ አካባቢው በሱማሌ ክልል ስር የሚተዳደር በሚመሰል ሁኔታ የሱማሌ ልዩ ኃይል እንደልቡ የሚፈነጭበት ሆኗል። አካባቢው 15 ቀን የተባለው ተረስቶ እስካሁን (9 ወራት) በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስና በኢሳ (ሱማሌ ልዩ ኃይል) የሚተዳደረ ስሆን በ5 km ሬድዬስ ላይ መሳሪያ የያዘ ሰው እንዳይገኝ ብሎ ያወጁትን በማጠፍ የአፋር አርብቶ አደሮች በአስፋልት ዳር በኢሳ ታጣቂዎች በመከላከያ ፊት ተገድሏል። ምንም የተባለ ነገር ግን የለም። አንድ አፋር ከሰመራ ተነስቶ ወደ አዋሽ የመጓዝ መብቱ ለ9 ወራት ተነፍጓል። ከቦታ ወደ ቦታ ኘንቀሳቀስ በገዛ ክልሉ የተነፈገው ብቸኛው ህዝብ የአፋር ህዝብ ይመስለኛል።

2.1. የአፋር ህዝብ ሁኔታ

የአፋር ህዝብ በዚህ ሁላ መከራ ውስጥ ሆኖ ያደረገው ነገር ብኖር ራስን መከላከልና ወደ ክልልና ፌዴራል መንግስት በተለያዩ መንገድ ቅሬታውን ማቅረብ ነው። ጥያቄው እንድሰ:ማ አንድ ጊዜ የኢትዬ ጅቡቲ መንገድ ዘግቶ የነበረ ብሆንም ምንም መፍትሔ ልያገኝ አልቻለም። ከትናነት ወዲያ እንደማንኛውም ጊዜ ኦብኖ ላይ በሰላማዊ ህዝብ ላይ በጅቡቲ መንግስትና በሱማሌ ክልል ጥምር ኃይል የተደረገው ጭፍጨፋን በተመለከተ በማህበራዊ ድረገፅ ባደረጉት ቅስቀሳ የብዙ ሚድያዎች ቀልቡ በመሳቡ መዘገብ ስጀምሩ የአገር መከላከያ አሳፋሪ የሆነ መግለጫ አውጥቷል።(በነገራችን ላይ የአፋር ክልል ፀጥታ ቢሮ፣ የክልሉ ህዝብ ግንኙነት እንድሁም የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ጥቃቱን የፈፀሙት የጅቡቲ ታጣቂዎች እንደሆነ በተለያየ ሚድያዎች ገልፇል። ) መከላከያው እስካሁን ዝምታ የመረጠው ሚድያ ትኩረት ያልሰጠው ሰለነበረ እንደሆነ ብንረዳም "የገዛ ዜጎችን ወንጀለኞች፣ የጅቡቲን መንግስት ደግሞ ንፁህ" ለማስመሰል የሄዱበት ርቀት የክልሉን ህዝብ በጣም አስቆጥቷል። መግለጫውን በመቃወም በሁሉም የክልሉ ከተሞች ከትናንት ጀምሮ ሰልፎች እየተካሄደ ይገኛል።

3. የሁለቱ መከላከያዎች ወግ

ሁሉም ኢትዬጵያዊ እንደሰማው የኢትዬጵያ መከላከያ "የአፋር ክልል መንገስትና የአፋር ህዝብን" ውሸታሞች ናችሁ እንጅ የጅቡቲ መንግስት እጅ የለበትም፤ ግጭቱ የግጦሽና የውሃ ነው ብሎ መግለጫ ስያወጣ የጅቡቲ መከላከያ በብኩሉ (በጀናራል ዘካሪያ በኩል) እንቅስቃሴው የአፋር ትሪያንግል ለመመስረት የሚደረግ ነው በማለት የአፋር ህዝብን በአገር ክህደት ወንጅሏል።

4. እንደ ማሳረጊያ

የሆነ ግዜ ላይ በአርጎባዎችና ኦሮሞዎች መሃል ግጭት ተነስቶ ለማስታረቅ የአፋር ሽማግሌዎች መሃል ይገባሉ። ሽማግሌዎቹ ከሁለቱም በኩል የቀረበው አቤቱታ ከሰሙ በኃላ አጥፊዎች ኦሮሞዎች መሆኑን ተረዱ። ነገር ግን የኦሮሞዎች ብዛትና ጥንካሬ ከአርጎባዎች አንፃር የማይመጣጠን ሰለሆነባቸው ለአርጎባ ከወሰኑ ግጭቱ ዳግሞ እንዳይነሳ ሰጉ። ሰለዚህም ወሰኑ። "mako lem oromooy, cakki qargobbal hayne" በማለት። ግርድፍ ትርጉሙ "ስህተቱ የኦሮሞ ነው፣ ካሳ ግን አርጎባዎች እንድሰጡ ወስንናል" እንደማለት። የአገር መከላከያ የጅቡቲ ጣልቃ ገብነት ጠፈቷቸው ሳይሆን ነገሮችን ከወደብ አንፃር ሰለሚመዝኑ "አጥፊዎች የጅቡቲ መንግስት ብሆንም ወቀሳውን ለገዛ ዜጎቹ" ቸረ። ሆነም ቀረም የአፋር ህዝብ እንደሁልጊዜው መሬቱንና ማንነቱን ለማስጠበቅ ያለውን አቅም በሙሉ እየተጠቀመ ለዘላለሙ ይኖራል።

ሰላም!

ምንጭ

1, ከማዋጥን ድህረ ገፅ
2, አፋር ቲቪ ድህረ ገፅ
3, በርበርታ ለትግል የሚጠቀምበት (Bafbarat siiti) ድህረ ገፅ
4, ተለያዩ ምንጮች