የከሸፈው የጠላት ስትራቴጅና ቀጣዩ ሴራ
(የአፋር ስነልቦና ከአለት የጠነከረ ነው!)
(ረጅም ፅሁፍ)
( Muhammed A. Yassen )
ማሳሰቢያ:
የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ ከሰሞኑ ክስተት ጋር ተያይዞ "አፋር በገዛ መሬቱ ራሱን እየተከላከለ ነው" ብዬ ድስኩር ለማቅረብ አይደለም። ሆን ብሎ ለመረዳት ያልፈለገና ፅንፍ የያዘ ካልሆነ በቀር ጉዳዩ ግልፅ ነውና። ወይም ደግሞ የአፋር_ኢሳ (ሱማሌ) ጦርነት ታሪካዊ ዳራ ለማስገንዘብ አይደለም። ይልቁንም የአፋር ህዝብ ባለፉት አራት አመታት እያፈለበት የመጣው ፋተናና እየበጣጣሰ የመጣው የጠላት ስትራቴጂ ከሰሞኑ የአንዳፎዖ ክስተት ጋር አያይዤ ለማሳየት ነው።
መቅደም:
ባለፉት አራት አመታት የአፋርን ሰላም ለማናጋት ሌት ቀን የሚሰሩ ሁለት ኃይሎች መኖራቸው ለሁሉም ግልፅ ይመስለኛል። እነርሱም የታላቋ ሱማሌ ህልመኞችና የዓባይ የትግራይ አቀንቃኞች። ( በጅምላ መፈረጅ እንዳይሆንብን ሁለቱን ኃይሎች በኢሳ ተስፋፊ ኃይልና የወያኔ ኃይል ተብሎ ቢወከል የተሻለ ነው። ከሱማሌ ወንድሞቻችንና ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደ ህዝብ ችግር የለብንምና።) ሁለቱም ኃይሎች የጋራ የሚያደርጋቸው ባህሪያቸው በ መሳሪያ ኃይል መተማመናቸውና ተስፋፊነታቸው ነው። የሚያገናኛቸው አላማ ደግሞ ለወደፊት ህልማቸው ለማሳካት እንደ ተግዳሮት የሚያዩት አፋርን ጠንካራ ሆና ማየት በመሆኑ አፋርን ማንበርከክ ወይም ማዳከም የሁል ጊዜ ሞኞታቸው ሙከራቸው ነው። ታዲያ "ባለፉት አራት አመታት" ያልነው ነባራዊ ሁኔታን ለማሳየት ያክል እንጅ ረጅም ታሪክ ያለው የቆየ ጉዳይ መሆኑን ከግምት እንድታስገቡ ይሁን።
(1) . መግቢያ:
ወያኔ አፋርን በተመለከተ ሁለት ስትራቴጂ በመቀየስ ወደ ስራ የገባው ገና ከሸገር ወደ መቀለ በተመለሱበትበት ሰሞን ነበር። አንደኛው ስትራቴጂ: አዘናግቶ ማጥቃት ይባላል: የዚህ ስልት ዋና አላማ ከተቻለ ከአፋር በኩል ቁልፍ ሰዎችን በመደለል አፋርን ከጎናቸው በማሰለፍ ከአጋሮች (ኢትዬጵያ: ብሔር ብሔርሰቦች) ጋር ማጋጨት ስሆን ካልሆነ ደግሞ አፋር ከማንም ጋር እንዳይወግን በማድረግ መጨረሻ ላይ መጠቅለል ነው። ሁለተኛው ስትራቴጂያቸው ደግሞ ከአፋር ጋር ግጭት ውስጥ ያሉትን በአሊያንስ በመጠቀም አፋርን በጦርነት ማንበርከክና በጦርንበት በሚደረሰባቸው ኪሳራ ተስፋ እንድቆርጡ ማድረግ ነው።
(2.1). የሁለቱ ስትራቴጂዎች አፈፃፀም
የመጀመሪያው ስትራቴጂያቸው የማስፈፀሚያ ስልታቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ላይ ሰለቆመ ገና በጅምሩ ነበር የከሸፈባቸው። “ከአፋር በኩል የተወሰነ የጎሳ መሪዎችና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች በጥቅም በመደለል ከጎናችን ካሰለፍን የአፋር ህዝብ በራሱ ጊዜ ከኛ ጎን ይሰለፋል” የሚል ከበፊት ጀምሮ ሰለ አፋር የያዙት የተሳሳተ ግንዛቤ ለይ በመንተራስ ያደረጉት ሙከራ ነው። የዚህ ስትራቴጂ ዋና አላማ አፋርን ከተቻለ ከጎን ማሰለፍ ካልተቻለ ቢያንስ ጦርነት ላይ እንዳይሳተፉ ማድረግ ስሆን ድል ስቀናቸው በስተመጨረሻ የአፋር መሬትና ሀብት ማዕከል ያደረገ ታላቋን ሀገረ መንግስት መመስረት ነበር። ሆኖም ግን እንደተሳሳቱ የገባቸው ዘገይቶ ነው። "ዓፋር ክወቅዐና?!" ብሎ ደብርፅዬን ቱግ ያለው ለዛ ነበር።
የመጀመሪያው እንዳልሰራላቸው እርግጠኛ ስሆኑ ሁለተኛው ስትራቴጂያቸው ነው የነደፉት። እሱም ከቆላ ተንቤን መልስ መቀሌን ስቆጣጠሩ!! ስትራቴጂው shock Doctrine ይባላል። መተግበሪያ ስልታቸው የአፋር ጠላት ከሆነው ከጅቡቲው ኢስማኤል ኡመር ጌሌ ጋር ጥምረት በመፍጠር የኢሳ (ሱማሌ) ኃይልን በመጠቀም ከፊትና ከኋላ በተመሳሳይ ግዜ ውጊያ በመክፈት የአፋር ኃይልን አጣብቂኝ ውስጥ ማስገባት ነው። የዚህ ስትራቴጂ ዋና አላማ ከስር እንደተያያዘው " አፋር Extensional treat እንድሰማው በማድረግ በኢትዬጵያ ላይ ተስፋ ቆርጦ የነፃነት ጥያቄ እንድያነሳና… የአፋር ትሪያንግል መመስረት ወደ ሚል ትግል እንድገባ ማድረግ ነው።" አፋርን ወደዚህ ተስፋ መቆረጥና የስነልቦና ውድቀት ማስገባት ከተቻለ የፈለጉትን ማሳካት እንደሚችሉ በመገምገም የነደፉት ስልት ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ይኼኛው ሰተራቴጂያቸው ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው በመተማመን ነው። በተለይ ከጅቡቲ መንግስት የሚፈልጉትን ነገር ማገኘት፣ ከሱማሌ ኃይሎች ጋር ታክቲካል አሊያንስ መፍጠር፣ የኢትዬ ጅቡቲን መሰመር በቀላሉ ለመያዝ፣ ወዘተ!
የጅቡቲው እስማዔል ኡመር ጌሌ በበኩሉ የዶር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በቀጠናው የመጣው የአሰላለፍ ለውጥ ስጋት የፈጠረበት ገና አጀማመሩ ላይ ነበር። በመሆኑም የሪፐፕሊካን ጋርዱ መሪ በሆነው ጀ/ መሀመድ ጃማዕ አስተባባሪነት በአፋር–ኢሳ (ሱማሌ) ግጭት ቀጠና ላይ የስልጠናና የትጥቅ ድጋፍ በማድረግ የጦርነት ቅስቀሳ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ኡንዳፎዖ ላይ የአፋር ባንድራ አውርዶ በማቃጠል "እኛ ሱማሌ እንጅ አፋር አይደለንም" በሚል መፈክር ጦርነት በይፋ እንድታወጅ አደርጎ ነበር። እዚህ ጋር መዘንጋት የሌለበት ነገር ቢኖር የታላቋ ሱማሌ ህልመኞችን በማስተባበር፣ ፋይናንስ በማድረግና ስትራቴጂዎችን በመቀየስ እንደ ጎበዝ አለቃ ሆኖ የሚያገለግለው የድሬዳዋ ተወላጁና የጅቡቲው ፕሬዝደንት እስማኤል ኡመር ጌሌ መሆኑ ነው። ሰለሆነም የእቅዱ አፈፃፀም ውስጥ ከመቅዲሾ እስከ ጅግጅጋ ብዙ አካላትን ያሳትፋል። የጅቡቲው በየአመቱ "Heritage" በሚል ስም የሚካሄደው ስብሰባ፣ በሱማሌ ክልል "ኣይሻ ላይ በየአመቱ የሚከበረው በአል" የዚህ ፕሮጄክት አካል ተደርጎ የሚወሰዱ ናቸው። የሱማሌ ክልሉ መስጠፌም የዚህ ህልም ተጠቂ መሆኑን ብዙ ማመሳከሪያ ማምጣት ይቻላል። በርግጥ በአማርኛ ስያወራ ብቻ ለሰማ ላይመስለው ይችላል።
(3). የወያኔ ወረራ፣ የእስማኤል ጌሌ ሰርግና ምላሽ
የወያኔ ኃይል በያሎ በኩል የመጀመሪያ ወረራ ስፈፅም በደስታ አቅሉን ከሳቱት ውስጥ በዋናነት የጅቡቲው እስማኤል ጌሌ ይጠቀሳል። የኢሳ (ሱማሌ) ኃይልን በማንቀሳቀስ በአምስት ግንባር ውጊያ እንድከፈት ለማድረግ ሳምንት አልፈጀበትም። በዚህ ብቻ አላበቃም። የወያኔ ኃይሎች ከውጭና ከውስጥ የሚያደርጉት ማንኛውም ግንኙት በማስተባበር ከሱዳን ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ይይዛል። ሚሌ የተቆጣጠሩ ስመስለው ወታደሮቹን ወደ አፋር ድንበር እስከ ማስጠጋት የደረሰ ደፋር ነው፣ እስማኤል። ኧረ ለምርጫ ውድድሩ "የአዋሽ ወንዝን ለስጦታ አበርክትላቸኃለሁ" ለማለትም ትንሽ ይሉኝታ አልያዘውም። ምን እሱ ብቻ ፤በጦርነት ጊዜ በነበረው ጫና ምክንያት የኢትዬጵያ መንግስት ከወደብ ጋር በተገናኘ ለኢስማኤል ያቀረቡት ጥያቄ በወሳኝ ሰዓት ውድቅ በማድረግ ከጠላት ጋር መወገኑን አስመስከሯል። ሆኖም ግን የአፋር ኃይል፣ እሱንና ወዳጆቹ እንዳሰቡት በቀለሉ የሚሰበር አልነበረምና በአንድ በኩል የኢሳ(ሱማሌ) ጥምር ኃይልን እየተከላከሉ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔን ሚሌን እየናፈቀው ወደ ቤቱ እንድመለስ ማድረግ በመቻሉ የእስማኤል ደም ግፊት ተነስቶ ለህክምና ከሀገር መውጣት ግድ ሆኖበት ነበር።
(4). ስትራቴጂው ስከሽፍ፤
የጅቡቲው እስማኤል ከግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ ሌላ አጋጣሚዎችን ከመጠበቅ አልቦዘነም። የኢትዬጵያ ፖሎቲካ በአስቸጋሪ ሁኔታ የገባ ስመስለው አጋጣሚውን ለመጠቀም ከመሞከር አይሰንፍም። በተለይ የኢትዬጵያ ጎሮሮ የሆነው ኢትዬ ጅቡቲ መንገድን የሽብር ቀጠና ለማድረግ ያላደረገው ሙከራ አልነበረም። የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ የመከላከያ አመራሮች፣ የአፋር ፀጥታ አካላት፣ የከባድና ቀላል መኪና ሹፌሮችና የአፋር አርብቶ አደሮች የዛ ሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ንፁኃን ናቸው።
እንደገና ሌላ እድል ሙከራ
የወያኔ ኃይል በሁለተኛ ዙር ወረራው ጭፍራን ይዞ ዞን አምስትን ስያጠቃ የኢሳ (ሱማሌ) ኃይል ጋር ኡንዳፎዖ ለመገናኘት ቀጠሮ ነበራቸው። በደዌ አድርጎ ወደ ኡንዳፎዖ ለመቆረጥ ያደረጉት ሙከራ የዛ ቀጠሮ ቦታ ለመድረስ ነበር። ሆኖም ግን እቅዳቸውን ቀድሞ ያወቀው የሀገር መከላከያና የአፋር ልዩ ኃይል መንገዱን ታሬና ላይ እንደዘጋባቸው ስያውቁ ወደ ሸዋሮቢት አቅጣጫ ለመመለስ ተገዶ ነበር። ያ ብቻ አይደለም የወያኔ ኃይል አፋርን ለሦስተኛ ዙር ስወር (ሰሜን ዞን) አጋጣሚውን ከመጠቀም የማይቦዝነው የኢሳ (ሱማሌ) ኃይል ጥቃት ፈፅሞ ነበር። የአፋር ህዝባዊ ኃይል ካለ ማንም እገዛ ሁለቱንም ኃይል እየተከላከለ መቋቋም በመቻሉ ያሰቡት shock doctrine ስልታቸው እንዳልሰራ ቢረዱም፤ ቢያንስ ኃይላቸውን ሰላዳከምን ከዚህ በኋላ የአፋር ኃይል ስጋት ልሆን ወደ ማይችልበት ደረጃ አድረሰናል የሚል ግምገማ ያደረገው የወያኔ ኃይልና በዛ ተማምኖ ውጊያ የከፈተው የኢሳ(ሱማሌ) አሸባሪ ኃይል ከኡንዳፎዖ መውጣቱን ስሰሙ ከጅቡቲው ኃይል ባልተናነሰ ደረጃ የወያኔ ኃይልም ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ገብቷል። የአፋር ስነልቦና ከአለት የጠነከረ የማይናወጥ የማይሰበር መሆኑን የገባቸው ዘገይቶ ነው።
(5) . ቀጠናዊ የኃይል አሰላለፍ ለውጥና የኢትዬጵያ ፖለቲካ
ዶር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጣ መንበረ ስልጣኑን ለመቆጣጠርና ለመደላደል የግድ የቀጠና ኃይል አሰላለፍ መቀየር ነበረበት። ከሱማሊያው ፌርማጆና ከኤርትሪያው ኢሳያስ ጋር በፍጥነት ጥምረት ማድረግ የተፈለገው ለዛ ነበር። ሚጢጢዬዋ ጅቡቲ ግን ጥምረቱን እንደ ስጋት በማዬት ከዚህ በተቃራኒ የተሰለፉት ኃይሎች ጎን ተሰለፈች። አልሲሲን ጋብዛ በአባይ ጉዳይ መግለጫ እስከ መስጠት ደረሰች። የሱማሊያ አሊያንስ ለመስበር አሸባሪዎችን በመደገፍ አለመረጋጋት ለመፍጠረ ሞከረች።
በተመሳሳይ መልኩ በአገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራት ትግራይ ወደ ዳር በመውጣቷ ተተኪ ያስፈልግ ነበር። "ኢትዬጵያኒስቱ" ሙስጠፌ ለዚህ ክብር ለመታጨት ወራት አልፈጀበትም። በመሆኑም የአፋር ሀጅ አወል ለዚህ ክብር ለመታጨት የወያኔ ጦርነት እስከሚነሳ መጠበቅ ነበረበት።
የወያኔ ጦርነት አፋርን ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም ብዙ ትሩፋት ደግሞ አስገኝቷል። ከትሩፋቶቹ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው አፋር በኢትዬጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ እንደ ጂኦግራፊዋ የመሀል ቦታ መያዝ መቻሏ ነው። ባለፈው ሳምንት ኡንዳፎዖ ነፃ ያወጣው የአፋር ኃይል፣ አፋርን ብቻ ሳይሆን ኢትዬጵያን ለማተራመስ የኢትዬ–ጅቡቲን መንገድንና አዋሽ ወንዝን መቆጣጠር ግቡ ያደረገው የአልሸባብ አሸባሪ ኃይል ህልም አከርካሪ የሰበረ ስሆን እንደ ሁልጊዜው ኢትዬጵያን ከውጭ ኃይል የመከላከል የዘውተር ተግባሩን ፈፅመዋል። ያም ሆነ ይህ ኡንዳፎዖ ነፃ በወጣች በማግስቱ ጠሚ ዶር አብይ አህመድ የሱማሌ ክልል ስንዴ ለመጎበኘት በሚል ሰበብ ጅግጅጋን ጎራ ያለው ለፕሬዝደንት ሙስጠፌ "አርፈህ ተቀመጥ!" የሚል ቀጭን ትዕዛዝ በጆሮው ሹክ ለማለት ነበር።
እስማኤል ኡመር ጌሌስ? በሂደት የሚናየው ይሆናል!!
(6). እንደ መውጫ
ኡንዳፎዖ ከአሸባሪዎች ነፃ መውጣቷን ተከትሎ ከሃርጌሳ እስከ መቅድሾ፣ ከጅግጅጋ እስከ ጅቡቲ፣ በየሚድያው ቅስቀሳ ተጧጥፈዋል። አላማቸው በተከፈተው ቀዳዳ ገብቶ አፋርን ብሎም ኢትዬጵያን ማተራመስ ስሆን የወያኔ ዳግሞ ወረራ እንድጀመር በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ። አፋር ደግሞ እንደ ሁልጊዜው በፈጣሪ ተመክቶ አገሩንና ክብሩን ላለማስደፈር በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ይገኛል።
ሰላም!
0 Comments